
ዲስ አበባ፡ ህዳር 13/2018 ዓ.ም
ኢ.ሥ.ኢ
ህዳር 14/2017 ዓ.ም ግዙፉና ውብ የሆነው የጥራት መንደር የተመረቀበት አንደኛ ዓመት በዓል በዛሬው ዕለት ተከብሮ ውሏል፡፡ በበዓሉ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ክቡር ካሳሁን ጎፌ /ዶክተር/ እንኳን ለሚያምረውና የኢትዮጵያን ደረጃ ለሚመጥነው የጥራት መንደር አንደኛ ዓመት የምረቃ በዓል አደረሳችሁ ያሉ ሲሆን የግቢው ማራኪነት፣ የህንፃዎቹ ውበትና የውስጥ አደረጃጃቶች የጥራት መንደር የሚለውን ስያሜ በትክክል የሚያሳብቅ ቢሆንም የጥራት መንደር ከሚያስብሉት ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ግን ኢትዮጵያ የጥራት ምልክት፣ የገቢና ወጪ ምርቶች ጥራት ቁጥጥር የሚጠበቅበት፣ በሀገራችን ሰማይ ስር ጥራንት ማስጠበቅ የሚችሉ የደረጃዎች ዝግጅት የሚከናወንበት፣ የተዘጋጁት ደረጃዎች መተግበራቸውን ቁጥጥር የሚደረግበት፣ በአጠቃላይ በተልዕኮ በእጅጉ የተሳሰሩ ተቋማት የሚገኙበት ግቢ መሆኑ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እንደ ክቡር ሚኒስትሩ ማብራሪያ የስራ ከባቢና የጥራት ጉዳይ የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ቀድመው የተረዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዐብይ አህመድ /ዶክተር/ ከዛሬ አስር ዓመት በፊት በሚያስገርም የዕይታ አድማስና ርቀት እንደዚህ አይነት የጥራት መንደር እንደሚያስፈልግና ጥራት በዚህ መልኩ ካልተጠበቀ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሊዋዥቅ ይችላል ብለው በነደፉት አቅጣጫና አርቆ አሳቢነት መሰረት ዛሬ በተግባር እንድናይ አድርገውናል፡፡ ይህም በመሆኑ ከተለመደው የተቆራረጠ አገልግሎት አሰጣጥ ወጥተን የተሟላ ስራ እንድንሰራ እድል ፈጥረውልናል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የግቢን ውበት ተጠብቆ ማቆየት የሁሉም የግቢው ማህበረሰብ ኃላፊነት መሆኑን ያስገነዘቡት ዶክተር ከሳሁን እንደ ውጫዊ ውበቱ ሁሉ በውስጥ አገልግሎት አሰጣጥም ቀልጣፋና ተገልጋይን የሚያረካ ስራ ለመስራት ከመቼውም ጊዜ በላቀ ቁርጠኝነት መዘጋጀት ይጠበቅባችኋል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው አስገንዝበዋል፡፡
በምረቃ በዓሉ ላይ የሚኒስትር መስሪያቤቱ አመራሮች፣ የጥራት መንደር ዳይሬክተሮችና የማኔጅመንት አባላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡